Macrovian Technology Logo
Telegram Icon
Back to insights
Technology
Transhumanism
AI
Future

ዕበየ ሰብእነት (Transhumanism)፡ ክፍል አንድ (፩) የጽንሰ ዐሳብ ትርጓሜ

Mikiyas Sima
Mikiyas Sima
CEO
May 12, 2025
5 min read
ዕበየ ሰብእነት (Transhumanism)፡ ክፍል አንድ (፩) የጽንሰ ዐሳብ ትርጓሜ

ዕበየ ሰብእነት (Transhumanism)፡ ምንድነው?

“Transhumanism” የተሠኘው የእንግሊዘኛ ቃል “Trans” እና “humanism” የሚሉትን የተለያዩ ቃላት በማጣመር ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው ከቴክኖሎጂ ጋራ በተገናኘ አልነበረም። ይልቁንም፣ በ1814 እንግሊዛዊው ጸሐፊ Henry Cary በ14ኛው ክፍለ-ዘመን በጣሊያናዊው ጸሐፊ ዳንቴ (Dante Alighieri) የተጻፈውን Divine Comedy የተሠኘውን ሥራ ወደ እንግሊዘኛ በተረጎመበት ወቅት፣ ዳንቴ ከሞት በኋላ የተለወጠ አካሉን (resurrected body) በምናቡ ያሰበበትን ሐሳብ ለመተርጎም ኹለት ቃላትን በማጣመር “Transhumanism” የተሠኘው ቃል ተጠቀመ።

ኾኖም በ1950ዎቹ Julian Huxley የተባለው እንግሊዛዊ የስሥነ-ሕይወት ተመራማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ “Transhumanism” የተሠኘውን ቃል ከቴክኖሎጂ ጋራ በማያያዝ፣ የሰው ልጆችን ተፈጥሮ በቴክኖሎጂ የማሻሻል እና በኹለንተናዊ መልኩ የላቀ የማድረግ እንቅስቃሴን እንዲወክልለት በማሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ቃል ተጠቀመ። በዚህም ምክንያት Huxley የ“Transhumanism” እንቅስቃሴ አባት ተደርጎ ይወሰዳል። እኛም ለዚህ ሐሳብ የዐማርኛ አቻ ቃል እንዲኾን በማሰብ “ዕበየ ሰብእነት” ብለን ተርጉመነዋል። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ “ዕበይ” የሚለውን ቃል፡ ልእልና፣ ከፍታ፣ ብልጫ፣ ክብር፣ ታላቅነት፣ ገናናነት፣ ብዛት፣ ጽናት ብለው ተርጉመውታል። በመኾኑም ከእንግሊዘኛው “Transhumanism” ሐሳብ አንጻር “ዕበየ ሰብእነት” ሰውን በቴክኖሎጂ ማግነን፣ ማተለቅ፣ ማክበር የሚለውን ሐሳብ ይወክላል።

እንደሚታወቀው፣ የሰው ልጆች ቶሎ ያረጃሉ፤ ረጅም እድሜ አይኖሩም፤ በሕመም ይማቅቃሉ፤ በተፈጥሮ አካለ ጎደሎ ኾነው ይፈጠራሉ፤ በብዙ በአደጋዎች ምክንያት አካሎቻቸውን ያጣሉ፤ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ስቃይ ውስጥ ያልፋሉ። ይኽ የሰው ልጆች ሕይወት ገጽታ ነው። ኾኖም እንደ ዕበየ ሰብእነት ትንታኔ፣ የዚኽ ኹሉ የሰው ልጆች መከራ መንስኤው የሰው ልጆች ተፈጥሮ ውሱን መኾን ነው ብለው ይሞግታሉ። ስለዚኽ፣ ዕበየ ሰብእነት፣ «የሰው ልጆች ለሥቃይ እና ለመከራ የተዳረጉት በተፈጥሯቸው ውሱንነት ምክንያት ነው» የሚል መሠረት ካለው ቅድመ ዕሳቤ (presupposition) የሚነሣ ፍልስፍና ሲኾን መሠረታዊው ጽንሰ-ሐሳቡ፣ የሰው ልጆችን ተፈጥሮ በቴክኖሎጂ በማሻሻልና በማዳቀል የሰው ልጆችን ልዕለ ኀያል የኾነ ዐቅምንና ችሎታን ማላበስ፣ መከራቸውንና ሰቆቃቸውን መቀነስ ነው።

የሰው ልጆች የማያረጁ (ቢቻል የማይሞቱ)፣ የላቀ አስተውሎት ያላቸው፣ በበሽታ የማይሠቃዩ፣ ለደስታቸው ገደብ ሊፈጥሩባቸው የሚችሉ እንቅፋቶችን በሙሉ በማስወገድ ኹልጊዜ ደስተኛ እንዲኾኑ ማድረግ እና በኹለንተናዊ መንገድ የሰው ልጆችን ሕይወት ማሻሻል (አለያም መለወጥ) ቀዳሚ ግቡ ነው። ዕበየ ሰብእነት፣ ይህን ዕቅዱን ለማሳካት ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (Artificial Intelligence) ጨምሮ እጅግ ብዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚጠቀም ሲኾን ጽንሰ-ሐሳቡ ግን ከሰው ሠራሽ-አስተውሎት ጋራ በእጅጉ የተለየ የምርምር ዘርፍ ነው። የሰው ሠራሽ አስተውሎት ግቡ የሰው ልጆችን ዐቅም ሰው ሠራሽ በኾነ አስተውሎት ማሳደግ፣ ከፍ ሲልም ንቃተ-ኅሊና (Consciousness) የተላበሰ የላቀ ሰው-ሠራሽ አስተውሎት (Artificial General Intelligence) በመፍጠር ከፍታን ለመያዝ የሚደረግ ጥረት በመኾኑ ከዕበየ ሰብእነት ጋራ ተቀራራቢ ግብ ቢኖረውም መንገዳቸው ግን ለየቅል ነው።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ ሥነ ሕይወታዊ ያልኾነ (Non-Biological) ሰው-ሠራሽ ሕይወት ለመፍጠር የሚደረግ ጒዞ ሲኾን፣ ዕበየ ሰብእነት በአንጻሩ፣ ሥነ ሕይወታዊ (Biological) የኾነውን የሰውን ተፈጥሮ በቴክኖሎጂ በማሻሻልና በማዳቀል የሰው ልጆችን ተፈጥሮ ራሱኑ ኀያል ማድረግ ነው። ኾኖም የዕበየ ሰብእነት ፕሮጀክት ሥነ ሕይወታዊ የኾነውን የሰው ተፈጥሮ፣ ንቃተ-ኅሊናን ብቻ በመውሰድ ሙሉ በሙሉ ሥነ ሕይወታዊ ባልኾነ መተካትን ሊጨምር ይችላል።

የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ አለማ የዕበየ ሰብእነት ትርጓሜን መዳሰስ ሲሆን በሌላ ጽሑፍ ስለ ዕበየ ሰብእነት ታሪካዊ ዳራ እንዲኹም በሰው ልጆች ላይ ሊፈጥር ስለሚችለው አዎንታዊ እና አሉታዊ ጎኖች በሰፊ ይዳሰሳል።

የህዳግ ማስታወሻ (ለዚህ ጽሑፍ እንዚህን ማጣቀሻዎች ተጠቅመናል) – Bibliography

  • Bostrom, N. “A History of Transhumanist Thought.” Journal of Evolution and Technology 14, no. 1 (2005).
  • Chardin, Pierre Teilhard de. The Phenomenon of Man. 1st edition. Harper Perennial Modern Classics, 2008.
  • Cole-Turner, Ronald, ed. Transhumanism and Transcendence: Christian Hope in an Age of Technological Enhancement. Washington, D.C: Georgetown University Press, 2011.
  • Huxley, Julian. “Transhumanism.” Journal of Humanistic Psychology 8, no. 1 (1968): 73–76.
  • Lennox, John C. 2084: Artificial Intelligence and the Future of Humanity. Grand Rapids, Michigan: Zondervan, 2020.
  • Mercer, Calvin R., ed. Religion and Transhumanism: The Unknown Future of Human Enhancement. Santa Barbara: Praeger, an imprint of ABC-CLIO, LLC, 2015.
  • ኪዳነወልድ ክፍሌ፣ “መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣” አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት 1948 ዓ.ም

Discussion

Share your thoughts or questions about this insight.

No comments yet. Be the first to respond.

Related Insights

Orwellian and Huxleyan Threats of Technology
Technology
Jul 15, 2025

Orwellian and Huxleyan Threats of Technology

Among the negative threats of technology, two perspectives known as Orwellian and Huxleyan have been thoroughly explored.

5 min read
Read more
ዕበየ ሰብእነት (Transhumanism)፡ ክፍል ኹለት (፪) ታሪካዊ ዳራ
Technology
Jun 1, 2025

ዕበየ ሰብእነት (Transhumanism)፡ ክፍል ኹለት (፪) ታሪካዊ ዳራ

በዚህ ጽሑፍ የዕበየ ሰብእነት (Transhumanism) ታሪካዊ ዳራ እና አመጣጥ በስፋት ተዳሷል።

5 min read
Read more
WhatsApp Icon