Macrovian Technology Logo
Telegram Icon
Back to insights
Technology
Transhumanism
AI
Future

ዕበየ ሰብእነት (Transhumanism)፡ ክፍል ኹለት (፪) ታሪካዊ ዳራ

Mikiyas Sima
Mikiyas Sima
CEO
June 1, 2025
5 min read
ዕበየ ሰብእነት (Transhumanism)፡ ክፍል ኹለት (፪) ታሪካዊ ዳራ

ዕበየ ሰብእነት (Transhumanism)፡ ታሪካዊ ዳራ

ክፍል አንድን ካላነበቡ፣ ቀድመው ክፍል አንድን እንዲያነቡ እንጋብዞታለን። «ዕበየ ሰብእነት (Transhumanism)፡ ክፍል አንድ (፩) የጽንሰ ዐሳብ ትርጓሜ» በሚል ርዕስ ያገኙታል

ዐዳዲስ ዐቅምና ችሎታን ለማግኘት መሞከር፣ በሕይወት ከሚገጥሙ እንቅፋቶችና ወሰኖች ዐልፎ ድንበሮችን የማስፋት ዝንባሌ የሰው ልጆች ባሕርይ ነው። ከጥንት ጀምሮ፣ ሰዎች ያለባቸውን ማኅበራዊ ገደብ፣ የሥፍራ ዉሱንነት ወይም አእምሯዊ ወሰን ጥሰው ለመኼድ ሲፈልጉ ኖረዋል። ለሕይወትና እና ለሰው ልጆች ደስታ ገደብ ወይም ዉስን ናቸው የሚሏቸውን ነገሮች ጥሰው ከፍታን ለማገኘትም ሲጥሩ ነበረ። ኾኖም ተፈጥሮ ካሰመራቸው ዉሱንነት የመሻገር ፍላጎቶች በጥንቱ ዘመን የተደበላለቁ ስሜቶችን የሚፈጥሩ ነበሩ። በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ የማኅበረ ሰብ ክፍሎች፣ አለመሞት ወይም ሕይወትን ለሺሕ አሊያም ለብዙ መቶ ዓመታት ማራዘም ይቻል እንደኾነ ሲያልሙ ቢኖሩም፣ የሰውን ተፈጥሮ በመቀየር የሚደረግ ሙከራ ግን የቅርብ ዘመን ጥረት ነው።

በተለይም፣ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን በምዕራቡ ዓለም የተነሣው ንቅናቄ የዓለምን አቅጣጫ አንዴ ላይመለስ እስከ ወዲያኛው ቀየረው። ይህ ንቅናቄ፣ ፍጥረታዊው ዓለም እንዲኹም የሰው ልጆች ሕይወትና ተፈጥሮ በሰው ልጆች የሚጠኑ የጥናት እና የምርምር መስኮች እንዲኾኑ አደረገ። ኾኖም፣ ይህ ዓለምንና የሰዎችን ሕይወት ለመረዳት የሚደረግ ጥናትና ምርምር፣ ከሃይማኖታዊው ሥልጣን (religious authority) ከሚሰጡ ትንታኔዎች ጋራ በግልጽ መጋጨት ጀመረ። ኾኖም ሃይማኖታዊው ሥልጣን በቀላሉ ሊረታው የማይችል ትልቅ ተግዳሮት ገጠመው።

ፍራንሲስ ቤኮን (Francis Bacon) በ1620 ያሳተመው “Novum Organum” የተሠኘው ጽሑፍ የሳይንስና የምርምር ስልት (scientific methodology) በተጨባጭ ምርመራ (empirical investigation) ላይ ብቻ የተመሠረተ እንዲኾን ቦይ በመቅደድ በዘመኑ ከተነሡ ሌሎች ፈላስፎችና ሳይንቲስቶች ጋራ ተደምሮ ሳይንስ እና ምርምር ሃይማኖታዊ ሥልጣን ላይ በይፋ ዐመፀ። በመኾኑም የሰው ልጆች፣ ዓለምን፣ የሰው ልጆችን ተፈጥሮና ሕይወት ለመረዳት ሃይማኖታዊ ሥልጣንን ከመከተል ይልቅ በተጨባጭ ምርመራ (empirical investigation) ላይ ትኵረት በማድረግ ሰዎች በአስተያየታቸው እና በፍርዳቸው ዓለምን እና ተፈጥሮን እንዲረዱ አደረገ።

በዚህ ንቅናቄ ምክንያት ትልልቅ የሳይንስ ምርምር ውጤቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። እንዲሁም እነዚህ የምርምር ውጤቶች የሰዎችን ሕይወት የሚያሻሽሉ እና ልፋትና ድካምን የሚቀንሱ በመኾናቸው ሰዎች ተስፋ እንዲጥሉባቸው አደረገ። የመድኀኒት ግኝቶች የሰውን ሕይወት ከበሽታና ሞት መታደግ፣ ፈጣን እና የተሻለ ትራንስፖርት፣ የሰዎችን ጉልበት የሚቀንሱ የኢንዱስትሪ ውጤቶች፣ ምቾት ያላቸው መገልገያዎች፣ መዝናኛዎችና እጅግ ብዙ የኾኑ ሳይንሳዊ ግኝቶች የሰው ልጆች መጻኢው ዘመን የተሻለ እንደ ኾነ ተስፋ እንዲያደርጉ፣ ሳይንስና ምርምር የተሻለ ዓለምን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ እንዲያምኑበት አደረገ።

በተጨማሪም የሰው ልጆች ራሳቸው ከሌሎች ፍጥረታት የተለዩ ሳይኾኑ፣ በዝርያ ብቻ የሚለዩ እኩል ፍጥረታት እንደኾኑ የሚሞግት ምሁራዊ ጉልበት በመፈጠሩ፣ የሰው ልጆች ተፈጥሮ፣ ከሌሎች ፍጥረታት እኩል ኑባሬያዊ (objectively) በኾነ መንገድ መጠናት ጀመረ። በተለይም ፈላስፋና የፊዚክስ ሊቅ የነበረው Julien Offray በ1770ዎቹ የሰው ልጆች ተፈጥሮ ከሌሎች ፍጥረታት እኩል ለፍጥረት ሕግ (laws of physics) ተገዥ ከኾነ፣ የሰው ተፈጥሮ ሌሎች ፍጥረታትን በምናጠናበት መንገድ መጠናት አለበት በማለት በመሞገቱ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል።

እንዲኹም በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የታተመው “On the Origin of Species" የተሠኘው የቻርለስ ዳርዊን (Charles Darwin) ጥናታዊ ሥራ ደግሞ የሰው ልጆች ስለ ሕይወት ያላቸው አመለካከት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳደረ። ዳርዊን፣ ሕይወት የቆመ ሳይኾን አኹንም በዝግመታዊ ለውጥ ኺደት ውስጥ እያለፈ ያለ (ever-evolving entity) እንደኾነ መተንተኑና ይህ ጥናት ተጽዕኖ በማሳደሩ ትልቅ መሠረት አኖረ።

እነዚህ ዕሳቤዎች በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ከፍ ወዳለ ደረጃ ከተሸጋገረው የህዋ ምርምር፣ ዘመናዊ ሕክምና፣ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ጋራ ተደምረው የሰዎችን ተፈጥሮ በመሠረታዊነት በማሻሻል (አሊያም በመለወጥ) ሰዎችን ደስተኞች፣ በሞት የማይጠፉ፣ የማያረጁ፣ የላቀ የማሰብ ችሎታ ያላቸው፣ ቀልጣፋ ቁመና ያላቸው በማድረግ ከተፈጥሮ ዉሱንነት በመውጣት የሰዎችን ሥቃይ እና መከራን ማጥፋት ወደሚል ፍላጎት አደገ።

እንደ J. B. S. Haldane፣ J. D. Berna፣ Bertrand Russell፣ Aldous Huxley የመሳሰሉ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ፈላስፎችና ሳይንቲስቶች፣ «የሰው ልጆች የግድ ተፈጥሯቸውን በቴክኖሎጂ በማዘመን ከፍታን መቀናጀት አለባቸው» በማለት ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የዕበየ ሰብእነት ምርምር መንገድ ጠራጊዎች ኾኑ። በመኾኑም፣ አኹን ላይ የሰውን ተፈጥሮ በቴክኖሎጂ የማሻሻል (ወይንም የመቀየር) ፕሮጀክቶች ቢሊየን ዶላሮች ይፈስስባቸውል።

የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ አለማ የዕበየ ሰብእነት ታሪካዊ ዳራ መዳሰስ ሲሆን በሌላ ጽሑፍ ዕበየ ሰብእነት በሰው ልጆች ላይ ሊፈጥር ስለሚችለው አዎንታዊ እና አሉታዊ ጎኖች በሰፊ ይዳሰሳል።

የህዳግ ማስታወሻ (ለዚህ ጽሑፍ እንዚህን ማጣቀሻዎች ተጠቅመናል) – Bibliography

  • Bostrom, N. “A History of Transhumanist Thought.” Journal of Evolution and Technology 14, no. 1 (2005).
  • Chardin, Pierre Teilhard de. The Phenomenon of Man. 1st edition. Harper Perennial Modern Classics, 2008.
  • Cole-Turner, Ronald, ed. Transhumanism and Transcendence: Christian Hope in an Age of Technological Enhancement. Washington, D.C: Georgetown University Press, 2011.
  • Huxley, Julian. “Transhumanism.” Journal of Humanistic Psychology 8, no. 1 (1968): 73–76.
  • Lennox, John C. 2084: Artificial Intelligence and the Future of Humanity. Grand Rapids, Michigan: Zondervan, 2020.
  • Mercer, Calvin R., ed. Religion and Transhumanism: The Unknown Future of Human Enhancement. Santa Barbara: Praeger, an imprint of ABC-CLIO, LLC, 2015.
  • ኪዳነወልድ ክፍሌ፣ “መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣” አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት 1948 ዓ.ም

Discussion

Share your thoughts or questions about this insight.

No comments yet. Be the first to respond.

Related Insights

Orwellian and Huxleyan Threats of Technology
Technology
Jul 15, 2025

Orwellian and Huxleyan Threats of Technology

Among the negative threats of technology, two perspectives known as Orwellian and Huxleyan have been thoroughly explored.

5 min read
Read more
ዕበየ ሰብእነት (Transhumanism)፡ ክፍል አንድ (፩) የጽንሰ ዐሳብ ትርጓሜ
Technology
May 12, 2025

ዕበየ ሰብእነት (Transhumanism)፡ ክፍል አንድ (፩) የጽንሰ ዐሳብ ትርጓሜ

በዚህ ጽሑፍ የዕበየ ሰብእነት (Transhumanism) ጽንሰ ዐሳብ ምንነት እና ትርጉም በስፋት ተዳሷል።

5 min read
Read more
WhatsApp Icon